በሕገወጥ የተያዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች በእጣ ይተላለፋሉ ተባለ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙና ዝግ ሆነው የተቀመጡ ናቸው ያላቸውን 21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች ለሆኑና በቋሚነት እየቆጠቡ ላሉ በእጣ እንዲተላለፍ መወሰኑን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ በትናንትናው፣ ጥር 22/2013 ዓ.ም እንዳስታወቁት የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ በህገወጥ ወረራ፤ ባለቤት አልባ ህንፃዎች፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፤ የቀበሌ መኖርያና ንግድ ቤቶችን አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት ላይ የተገኙ ግኝቶች ላይ ውሳኔ አስተላለፏል።
የ Twitter ይዘት መጨረሻ, 1
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ባለቤት አልባ ህንፃዎች እንዲሁም የጋራ መኖሪያና የቀበሌ ቤቶች ዙሪያ የተደረገ የማጣራት ውጤትን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ ይፋ መማድረጋቸው ይታወሳል።
ምክትል ከንቲባዋ ማክሰኞ ዕለት ይፋ ባደረጉት የጥናት ውጤት 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በሕገ-ወጥ የተወረረ መሆኑን፣ 21 ሺህ 695 የጋራ መኖርያ ቤቶች በተለያየ በሕገ-ወጥ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን፣ 322 ግንባታቸው ያለቀና ያላለቀ ህንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን፣ 14 ሺህ 641 መኖርያና ለንግድ የተከራዩ የቀበሌ ቤቶችን ያለ አግባብና በሕገ-ወጥ ይዞታነት የሚገኙ መሆኑን አስታውቀው ነበር
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ማክሰኞ እለት፣ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ 13 ሚሊዮን 389 ሺህ 955 ካሬ ወይም 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በሕገ-ወጥ መያዙን አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት በሕገወጥ መንገድ የተያዙ እና ዝግ ሆነው የተቀመጡ 21 ሺህ 695 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎች እና በቋሚነት እየቆጠቡ ላሉ ነዋሪዎች በእጣ እንዲተላለፍ የከተማዋ ካቢኔ ወስኗል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በተጨማሪም በጥናቱ የተገኙ 322 ባለቤት አልባ ህንጻዎች የከተማ አስተዳደሩ እንዲወርስ እና በግልፅ ጨረታ እንዲሸጡ ውሳኔ ማሳለፉን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን በተመለከተም በህገ-ወጦች የተያዙ የመኖርያ ቤቶች ግልፅ የሆነ መስፈርት ወጥቶላቸው ለአቅመ ደካሞችና ለተለያየ ችግር ለተጋለጡ የከተማው ነዋሪዎች እንዲሰጥ፤ ንግድ ቤቶቹም ቢሆኑ በህገ-ወጥነት ከያዙት ቤቶች አስለቅቆ ለስራ አጥ ወጣቶች በእጣ እንዲከፋፈል መወሰኑን አስታውቋል።
ይህ እስኪከናወን ድረስ ግን ቤቶቹ ባሉበት ታግደው እንዲቆዩ ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ውሳኔውን ማሳወቅ እንዳለባቸው መወሰኑን ምክትል ከንቲባዋ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስታውቀዋል።
በከተማዋ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ባህሪያት ጋር በተያያዘ በህገወጥ መንገድ ባዶ የሆነ የመንግስትን መሬት በወረራ በመያዝ የተፈፀመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ይህ ድርጊት በግለሰብ ደረጃና በሀይማኖት ተቋማትም ጭምር የተፈፀመ መሆኑ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተባባሰ የመጣ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ እንዳለ ባካሄድኩት ጥናት ደርሼበታለሁ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
0 Comments