በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ ጥር 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚደረገው ጥረት ጋዜጠኞች ትኩረት ሰጥተው በመስራት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ። በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻ ላይ ሙያዊ ድጋፍ ላደረጉ ጋዜጠኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ዕውቅና ከተሰጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮችና የካሜራ ባለሙያዎች ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች እንዳሻው ሹሜ፣ የሰራው ወርቁ፣ አዲሱ ረታ፣ አሸናፊ በድዬ፣ ሃይለእየሱስ ተፈራ ሲሆኑ የካሜራ ባለሙያዎች ደግሞ አብርሃም ክንፈ፣ ነፃነት ሙሉዓለም፣ ዳንኤል ሙሴ፣ ብዙአየሁ ብርሃኑ እና ሙላቱ መሰረት ናቸው። ሹፌሮች፣ በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ሚዲያ ተቋማትን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሄዱ የቴክኒክ ቡድን አባላትም እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ ግንባር በመገኘት የዘገቡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ አማራ መገናኛ ብዙሃን፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ዋልታ መረጃ ማዕከልና ከግል ሚዲያ ደግሞ የኢሳት ቴሌቪዥን እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ናቸው። ለጋዜጠኞቹ የተሰጠው እውቅና እስካሁን ላበረከቱት ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይ በአገሪቷ ላሉ ትላልቅ አጀንዳዎች ተጨማሪ ኃላፊነት ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደተናገሩት፤ በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት መገናኛ ብዙሃን በተቀናጀ መንገድ መስራታቸው ትክክለኛ መረጃ ለኢትዮጵያም ለዓለም ህዝብም እንዲደርስ አድርጓል። "ሰራዊቱ የፈጸመውን የጀግንነት ተግባር በስራችሁ ማሳወቃችሁ የሚያኮራና የሚያሰመስግን ተግባር ነው" ብለዋል። አሁን ቀጣዩ የቤት ስራ የትግራይ ህዝብ ምን ያስፈልገዋል? የሚለውን በትኩረት በመለየት ለመንግስትም እንዲደርስ ማድረግ መሆኑን ተናግረው፤ "በክልሉ የሚቀርቡ ሰብአዊ እርዳታዎች በተገቢው መንገድ እንዲደርስ ሙያዊ ኃላፊነታችሁን በብቃት መወጣት አለባችሁ" ብለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ባለሙያዎች በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የመድሃኒት፣ ምግብና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎች መድረሳቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝቧል። በተለይም በቀጣይ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች መኖራቸውን አስታውሶ ግብርና፣ ገበታ ለአገርና ምርጫ ላይ በትኩረት እንዲሰሩም ጠይቋል። የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሰሃ ወልደሰንበት በበኩላቸው የጁንታው ቡድን በተለይም መጀመሪያ አካባቢ የተሳሳቱ መረጃ ያሰራጭ እንደነበር አስታውሰዋል። "በስፍራው የተገኙ ባለሙያዎች ግን ከቦታው ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ህብረተሰቡ እንዳይደናገር በማድረግ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል" ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እንደተናገሩት፤ በዘመቻው ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለህዝቡ መረጃ ማቀበላቸው የመገናኛ ብዙሃንን ተአማኒነት ከፍ አድርጓል። በዘመቻው ላይ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የተሰጠው እውቅና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከቤይ ኢትዮጵያ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።